ሱመር
ከWikipedia
ሱመር (ወይም ሹመር፣ ሳንጋር፣ ሰናዖር) በጥንታዊ መካከለኛ ምሥራቅ አለም በቅድሚያ ሥልጣኔ የሚባል ኹኔታ የደረሰለት አገር ነበር። ዘመኑ ከታሪካዊ መዝገቦች መነሻ ጀምሮ ይታወቃል። 'ሱመራዊ' ማለት ሱመርኛ የቻሉ ወገኖች ሁሉ ነው። ከጥንታዊ ግብፅ እና ከሕንዶስ ወንዝ ሸለቆ ሥልጣኔ ጋራ ከሁሉ መጀመርያ ሥልጣኔ ካሳዩት አገሮች አንዱ ነው ይባላል።
[ለማስተካከል] ስም
ሱመሩ የሚለው ስም በጎረቤቶቻቸው በአካድ ሰዎችም ሲጠራ ሕዝቡ ለራሳቸው የነበራቸው ስም ሳግ-ጊ-ጋ (ጥቁር ራስ ያላቸው) ነበር። አገራቸውንም ኪ-ኤን-ጊር ይሉት ነበር። በተረፈ በኬጢያውያን መዝገቦች አገሩ ሳንሃር፣ በግብጽ አማርና ደብዳቤዎች ሳንጋር፣ በመጽሐፍ ቅዱስም ሰናዖር ይባላል።
[ለማስተካከል] ታሪክ
ጽሕፈት በመፍጠሩ የታሪክ መጋረጃ ሲከፈት፣ ሱመራውያን በደቡብ ሜስጶጦምያ (ከጤግሮስና ኤፍራጥስ ወንዞች መኃል፣ የዛሬው ኢራቅ) ይገኙ ነበር።
ጥንታዊው የሱመራውያን ነገሥታት ዝርዝር የያንዳንዱን ከተማ ሥርወ መንግሥት ይዘርዝራል። ከነዚህም በመግቢያው ያላቸው ነገሥታት ከማየ አይህ በፊት እንደ ነገሡ ይላል። እነዚህ ስሞች ትውፊታዊ ሊሆኑ ይችላል። ከሌላ አፈ ታሪክ ምንጭ መጀመርያ የተገኘው ስም በዝርዝሩ የኪሽ ንጉሥ ኤታና ነው። ከዚያ በኋላ የኤንመርካርና የልጁ ልጅ የጊልጋሜሽ ስሞች ይታያሉ። እነዚህ በኡሩክ እንደነገሡ ይገልጻል። ከሥነ ቅርስ የታወቀው መጀመርያ ስም የኪሽ ንጉሥ ኤንመባራገሲ ነው። እሱ ደግሞ የጊልጋሜሽ ትውፊት በተባለ ጽሑፍ ስለሚገኝ ይህ ለጊልጋሜሽ ታሪካዊ ሕልውና ምናልባትነት መስጠቱ ይታመናል።
የአዳብ ንጉሥ ሉጋል-አኔ-ሙንዱ በዘመቻ እስከ ሜዲቴራኔያን እና እስከ ጣውሮስ ተራሮች (ትንሹ እስያ) ና እስከ ዛግሮስ ተራራዎች (ፋርስ) ድረስ እንዳቀና ይመዘገባል። ከዚህ በኋላ የላጋሽ ንጉሥ ኤ-አና-ቱም ሱመርን ሁሉ ኤላምንም በከፊል አሸንፎ እሱ ላይኛ ንጉስ ሆነ። ከተገኙ ጽላቶች መሠረት፣ የሱ መንግሥት አደራረግ ተገዥ ወገኖችን ማስፈራራትና ግፍ መሆኑን ልንገምት እንችላለን። የላጋሽ ንጉሥ ኡሩካጊና የራሱን ሕገጋት አውጥቶ ለድኆች ማሻሻል አደረገ፤ በተጨማሪ 1 ሚስት ቀድሞ ብዙ ባሎችን የምታገባበትን ልማድ ከለከለ።
ከዚያ ቀጥሎ የኡማ ንጉሥ ሉጋል-ዛገ-ሲ ላጋሽን አገለበጠውና ዋና ከተማውን በኡሩክ አድርጎ መንግስቱን ከፋርስ ወሽመጥ እስከ ሜዲቴራኔያን ድረስ አስፋፋ።
ከሉጋል-ዛገ-ሲ ላይኛነቱን የያዘ ሱመራዊ ሰው ሳይሆን የአካድ ንጉሥ 1 ሳርጎን ነበር። የአካድ ሰዎች ሴማዊ ቋንቋ፣ አካድኛ ይናገሩ ነበር። ቋንቋቸውን በሱመር እንዲሁም በኤላም ይፋዊ በግድ አደረጉ። በጽላት ዜና መዋዕል መዝገቦች መሠረት፣ ሳርጎን የባቢሎንን ሥፍራ ወደ አካድ ዙሪያ አዛወረ።
የአካድ መንግሥት በጉታውያን ዕጅ ከወደቀ በኋላ የላጋሽ ንጉሥ ጉዴአ ተነሣ። ከዚያ በኋላ የኡር ንጉስ ኡር-ናሙ ላጋሽን አሸንፎ ላይኛነቱን ያዘ። እሱ በተለይ የኡር-ናሙ ሕገጋት ስለ ተባለው ፍትኅ ይታወሳል። በዚህ ወቅት ብዙ ሴማዊ ቋንቋ ያላችው አሞራውያን ወገኖች ወደ ሜስጶጦምያ ስለ ገቡ፣ የሱመርኛ ጥቅም ቀስ በቀስ ቀነሰ። ሆኖም ሱመርኛ በትምህርት ቤትና በሃይማኖት ረገድ ይቀጠል ነበር።
ይህ የኡር መንግሥት እስከ 2012 ክ.በ. ኤላማውያን እስከ ወረሩት ድረስ ቆየ። የዚያ ውጤት አሞራውያን ለራሳቸው ከተሞች ያዙና የሱመር ሃይል ጠፋ። ከነዚህ ከተሞች መካከል ባቢሎን በንጉስዋ ሃሙራቢ ወቅት ላይኛነቱን ለረጅም ወራት መሰረተች።