ሚስቶች በኖህ መርከብ ላይ
From Wikipedia
ከማየ አይህ በፊት በነበሩ ዕለታት ስለ ኖሩ በኖህ መርከብ ላይ ስለ ተገኙ ስለ አራቱ ሴቶች ኦሪት ዘፍጥረት ምንም እንኳን ዝም ቢል፣ ከሌላ ምንጭ ስለነዚሁ ሴቶችና በተለይ ስለ ስሞቻቸው የተገኘው አፈ ታሪክ በርካታ ነው።
በጥንታውያን እምነት ዘንድ፣ የሴም፣ የካምና የያፌት ሚስቶች ዕጅግ የረዘማቸው ዕድሜ ሲኖራቸው ከመጠን ይልቅ ለብዙ መቶ ዓመታት ኑረው ለያንዳንዱ ትውልድ ትንቢት እየተናገሩ ኖሩ። እነኚህ ሲቡሎች ተብለው ለግሪኮች ለሮማውያንም እንደ ቅዱሳን መጻሕፍት የተቆጠሩ የሲቡላውያን መጻሕፍት ደራሲዎች እንደ ነበሩ ታመነ። የሮማውያን ቅጂ በ397 ዓ.ም. አካባቢ በእሳት ተቃጥሎ ዛሬ የሚታወቁ የሲቡላውያን ንግሮች የተባሉት ሰነዶች ኦሪጂናል መሆናቸው ለምሁሮች አይመስላቸውም። ከመጀመርያ ሲቡሎች በኋላ ሌሎች ሲቡሎች እንደ ተከተሉ ለንግሮቹም እንደ ጨመሩ ይታስባል።
በመጽሐፈ ኩፋሌ የሴም፣ የካምና የያፌት ሚስቶች እንዲሁ ተብለው ይሰየማሉ፤
- የሴም ሚስት፣ ሰደቀተልባብ
- የካም ሚስት፣ አኤልታማኡክ (ወይም በለላ ትርጉም ናኤልታማኡክ)
- የያፈት ሚስት፣ አዶታነሌስ (ወይም በለላ ትርጉም አዳታነሥስ) ናቸው።
ከዚህ በላይ ሦስቱ የኖህ ልጆች ከጥቂት ዓመት በኋላ ከአራራት ሠፈር በየአቅጣጫው ሂደው ለሰው ልጆች ሁሉ እናቶቻቸው ለሆኑት ለሚስቶቻቸው ስሞች የተባሉ 3 መንደሮች እንደ መሠረቱ ይታረካል።
በኋላ ዘመን የክርስቲያን ጸሓፊ ቅዱስ አቡሊድስ (227 ዓ.ም. የሞቱ) በሶርያ ታርጉም ዘንድ ለዚህ ተመሳሳይ የሆነ ታሪክ አወሩ። ነገር ግን የሴምና የካም ሚስቶች ስሞች እንዳለዋወጡ ይመስላል። እሱ እንዲሁ "የኖህ ልጆች ሚስቶች ስሞች አንዲሁ ናቸው፤ የሴም ሚስት፣ ናሃላጥ ማህኑክ፤ የካምም ሚስት፣ ዘድካት ናቡ፣ የያፈትም ሚስት አራጥካ ይባላሉ" ብሎ ጻፈ።
ጆን ጊል (1697-1771 እ.ኤ.አ.) በመጽሓፍ ቅዱስ ነክ አስተያይቶቹ ስለ አንድ የዓረብ አፈ ታሪክ የጻፈው እንዲሁ ነው፤ "የሴም ሚስት ስም ዛልበጥ ወይም ዛሊጥ ወይም ሳሊትሲሆን፣ የካምም ድግሞ ናሓላጥ ተባለች፣ የያፌትም ደግሞ አረሢሢያ ተባለች።
በ'ሲቡላውያን ንግሮች' ዘንድ፣ ከሲቡሎቹ የአንዲቱ ስም ለዛልበጥ ተመሳሳይ ነበረች፤ እሷም የ"ባቢሎን ሲቡል" ሳምበጥ ነበረች። ከጥፋት ውሃ 900 አመት በኋላ ወደ ግሪክ አገር ሄዳ የንግሮች ጽሑፍ እንደ ጀመረች ብላ ጻፈች። ከዚያ በላይ የጻፈችው ጽሁፍ ከማየ አይህ አስቅድመው የኖሩት የቤተሠቧ ስሞች ይታርካሉ። እነሱም አባቷ ግኖስቲስ፣ እናቷ ኪርኬ፤ እህቷም ዒሲስ ናቸው።
በከለዳዊው በቤሮሱስ ዘንድ (ከክርስቶስ በፊት በ280 ዓመት ያህል የጻፈ) የልጆቹ ሚስቶች ፓንዶራ፣ ኖኤላ፣ ኖኤግላ ተብለው ተሰየሙ።
በአይርላንድ አፈ ታሪክ ስለ ሦስቱ ልጆችና ስለ ሚስቶቻቸው የሚተረተው ብዙ አለ። በዚሁ ምንጭ ሚስቶቹ ኦላ፣ ኦሊቫ፣ ኦሊቫኒ ይባላሉ። እነኚህም ስሞች የተወሰዱ ኮዴክስ ጁኒየስ ከተባለው ጥንታዊ (700 ዓ.ም.) እንግሊዝ ብራና ጥቅል ይመስላል። ይኸው ጽሕፈት እንደ ረጅም ግጥም ሆኖ በገጣሚው በካድሞን እንደተጻፈ ይታሥባል።
የሀንጋሪ አፈ ታሪክ ደግሞ ስለ ያፌትና ኤነሕ ስለ ተባለችው ስለ ሚስቱ አንዳንድ ተረት አለበት። ይህ መረጃ የሚገኘው የአንጥያኮስ ጳጳስ ሲጊልበርት ከተጻፉት ዜና መዋዕል እንደ ሆነ ይባላል።
ከ1618 ዓ.ም. ብቻ በሚታወቀው "ያሻር መጽሐፍ" በሚባለው ጽሕፈት ዘንድ፣ አንዲሁም ባንዳንድ የአይሁድ መምሁራን ዘንድ፣ የኖህ ሚስት ስም የቃየል ልጅ ናዕማህ ተባለች። ነገር ግን ጥንታዊ መጽሀፈ ኩፋሌ ስምዋ አምዛራ ተብሎ ይሰጣል። "ናዕማህ" የሚለው የካም ሚስት ስም ለኖህ ሚስት ስም በአይሁድ ልማድ እንደ ተሳተ ጆን ጊል ሐሳቡን አቅርቧል።